አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ሜጋ አምፊ ትያትር ቤትን ሊያስተዳድር ነው

Posted by Addismood on Monday, June 21, 2010 Under: Music
ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እና የኢትዮጵያ ጃዝ ሙዚቃ አባት የሆነው አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ በጋራ በመሆን አዲስ ኩባንያ ያቋቋሙ ሲሆን፣ ይህ ኩባንያ ሜጋ አምፊ ትያትር ቤትን ያስተዳድራል፡፡
ሁለቱ አካላት የሚያቋቁሙት ኩባንያ ዋል አፍሪካ ጃዝ መንደር የሚል ስያሜ ያገኘ ሲሆን፣ ማን ምን ያህል ድርሻ ይኑረው የሚሉ ጉዳዮችን በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ተጠናቀው ኩባንያው ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፍቃድ እንደሚያገኝ አርቲስት ሙላቱ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልጸዋል፡፡

አዲሱ ኩባንያ የሚያስተዳድረው ሜጋ አምፊ ትያትር፣ በማዕከላዊው አዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ፣ ቸርቸር ጎዳና ላይ ከቴዎድሮስ አደባባይ ፊት ለፊት ይገኛል፡፡ ይህ ትያትር ቤት በኢትዮጵያ የመጀመርያው ፊልም ቤት የሆነውንና በቀድሞ ስያሜው ሰይጣን ቤት እየተባለ የሚጠራውን አምፊ ትያትር ቤትን ያጠቃለለ ነው፡፡

ትያትር ቤቱ ቀደም ሲል ይተዳደር የነበረው በሜጋ ኢንተርፕራይዝ ሥር ሲሆን፣ ውጤታማ ባለመሆኑ እና በተለያዩ ጉዳዮች ትያትር ቤቱን ሲያስተዳድር የቆየው ሜጋ ሥራውን እንዲለቅ ከተደረገ በኋላ ንብረቱን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዲረከበው ተደርጓል፡፡

ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በ1987 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን፣ ኩባንያው የአገሪቱን የኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም፣ ባህል እና ኪነጥበብ ለቀሪው ዓለም በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ሥራው ከ42 ዓመታት በፊት የኢትዮ-ጃዝ ሙዚቃን ከፈጠረው አርቲስት ሙላቱ ጋር ሊያገናኘው እንደቻለ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ይገልጻሉ፡፡

በቀጣይነት በሁለቱ አካላት የተመሠረተው ኩባንያ የብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃ እና ባህል በአምፊ ትያትር ቤቱ ያቀርባል፣ የጃዝ ሙዚቃ ት/ቤት ይከፍታል፣ ልዩ ልዩ ዶክሜንታሪ ፊልሞችን በፊልም ቤቱ የማሳየትም ዕቅድ ነድፏል፡፡

ይሁንና ትያትር ቤቱም ሆነ አምፊ ትያትር ቤቱ አሁን ያሉበት ይዞታ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በመሆኑ፣ አዲሱ ኩባንያ እስከ ሰባት ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ ትያትር ቤቱን እና ፊልም ቤቱን በአዲስ መልክ በድጋሚ ለማደራጀት ዕቅድ መያዙን አርቲስት ሙላቱ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ይህ ገንዘብም በሁለቱ አካላት መዋጮ እንዲሁም ከውጭ አገራት በሚገኝ ፋይናንስ ለመሸፈን መታቀዱን አርቲስት ሙላቱ ጨምሮ ገልጿል፡፡

የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሻለ በልሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አቶ ሙላቱ ትልቅ የኪነ ጥበብ ሰው በመሆኑ የጥበብ ማዕከሉን የላቀ ደረጃ ላይ ያደርሰዋል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡ በሜጋ የአስተዳደር ወቅት የነበረው ሥራ በአሁኑ ሰዓት ኦዲት እየተደረገ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር

In : Music 



blog comments powered by Disqus

Categories

Make a Free Website with Yola.