የኢትዮጵያ ቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር፣ አዲስ አበባ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የዘፈኖችን፣
የፊልሞችን እና ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎችን አባዝተው እና አስመስለው ሠርተው በመሸጥ ሥራ የተጠረጠሩ 108 ሙዚቃ
ቤቶችን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በትናንትናው ዕለት ሕጋዊ ፍተሻ ለማድረግ ማቀዱን ገልጿል፡፡
የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዕቁባይ እንደተናገሩት፣ ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ችግሩን ለመፍታት
ከስድስት በላይ ከሆኑ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አጋር የሙያ ማኅበሮች ጋር በመሆን ሲንቀሳቀስ የቆየ ቢሆንም፣ ችግሩን
ሙለ ለሙሉ ለማስቀረት አልተቻለም፡፡
ከዚህ ቀደም በጎንደር እና በደሴ ከተሞች በተደረገው አሰሳ፣ በመቶ
ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሕገ ወጥ የኪነ ጥበብ ውጤቶች መገኘታቸውን ኃላፊው ገልፀው፣ በተለይ በጎንደር ከተማ በሕገ ወጥ
መንገድ ሲያባዙና ሲሸጡ የነበሩ ግለሰብን ሕግ ፊት በማቅረብ በ6 ዓመት እሥራት እንዲቀጡ ተደርገዋል፡፡ አዲስ አበባ
ውስጥም ችግሩ በሰፊው በመንሰራፋቱ አሰሳ ለማድረግ እንደተገደዱ ተናግረዋል፡፡
ትናንትና ሕትመት
ከመግባታችን በፊት በከተማዋ በተደረገ ፍትሻ፣ ከ31 በላይ የማባዣ ማሽኖች እና ሕገ ወጥ ቅጂዎች መገኘታቸውን አቶ
ዕቁባይ ገልፀው፣ በተለይ በመስኪድ አካባቢ 46 ሕገ ወጥ ሱቆች የአገር ውስጥ እና የውጭ የጥበብ ውጤቶች በብዛት
እንደተገኙና ማባዣ ማሽኖችንም በመያዝ ላይ መሆናቸውን ሊቀመንበሩ ገልፀዋል፡፡
ፍተሻውን በአዲስ አበባ
ማድረግ ከሌሎቹ ከተሞች በበለጠ ከባድ እንደሚያደርገው የሚናገሩት አቶ ዕቁባይ፣ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት
የማባዣ ቦታዎቹ ከከተማዋ ውጭ፣ መሸጫ ሱቆቹ ደግሞ ከተማ ውስጥ በመሆናቸው በቀላሉ ለመሰወር አመቺ በመሆኑ ነው፡፡
ተጠርጥረው
ሱቆቻቸው እየተፈተሹ ከሚገኙት ሙዚቃ ቤቶች መካከል፣ ትላልቆቹና ታዋቂዎቹ እንደሚገኙበት አቶ ዕቁባይ ገልፀው፣
ስሞቻቸውን በቅርብ ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ሕገ ወጥ የማባዛት ሥራ እንደሚያከናውኑና እንደሚሸጡም በሙዚቃ
ቤቶቹ ላይ ባደረጉት ክትትል እንደደረሱበት ተናግረዋል፡፡
በተደረገው ድንገተኛ የፍተሻ ሥራ ብዙ ቁጥር
ያላቸው በሥራው ላይ ተሰማርተው የነበሩ የሱቆች ባለቤቶችን በቁጥጥር ሥር ለመዋል መቻላቸው ተገልጿል፡፡
በአዲስ
አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ በአሁኑ ሰዓት ከ2 ሺሕ በላይ ሕገ ወጥ ሱቆች እና ከአራት ሺሕ በላይ ሕገ ወጥ አዟሪዎች
የጥበብ ውጤቶችን በማከፋፈል ላይ እንደሚገኙ ጥናቶች እንደሚያመለክቱ አቶ ዕቁባይ አብራርተዋል፡፡
ሪፖርተር
In : Music
blog comments powered by