Posted by Basha BIRU on Sunday, February 14, 2010
Under: Poems
ስሚኝማ!
እንዲህ ያለ አበባ አለ?!
እንዲህ ያለ እጽዋት አለ:እንዲህ ያለ የአበባ ዘር?
ካፈር ከምድሩ ተላቆ:ስርሽ ቅርንጫፍሽ ባየር
እንደ ወፍ ውበት ተንሳፎ ባላፊ አግዳሚ እየታየ
ውሎሽ ከነፋስ ጋር ብቻ መሆኑ ይፋ እየለየ
እንዲህ ያለ አበባ አለ?
ካገር ከሰው ተለይተሽ
ከሲሳይ ከውሃሽ ርቀሽ
እውነትሽን አውጥተሽ ቀብረሽ
ሁለመናሽን አየር ላይ አስጥተሽ ያይን-አዋይ ሆንሽ
ቅርብ ሁነሽ እንደሩቅ ራእይ:ያው ተንሳፈሽ ትታያለሽ::
ቅጠልሽ ገና አልደረቀም
ያበባ ወዝሽ አልጠፋም
ግን ውዷ ውብ ጽጌረዳ እውን ዛሬም አበባ ነሽ?
ነው መልክ አይጠወልግም ልብ ነው ጠውልጎ እሚረግፍ
ፍቅርን ከነቀየው ነቅሎ ተስፋ ከአንጀት ነው እሚገፈፍ!!
አሁን እውነት ከጥንት አፈር
እትብት ወጥቶ እንደ አዲስ ያምራል
የአንገት-ሃብል ሆኖ ይጠልቃል?
እንደ እጅ-አንባር ይታሰራል?
ስርሽ ከምድር በላይ ውሎስ አበባነትሽ ይቆያል?
የመልክሽና የመልኬ ጥቁር ብርሃን ሲንጣለል
በአሳር እንደጫሩት እሳት በአደባባይ ሲንበለበል
ያን የማንነት ኦና የአገር-አልቦነትን ሚስጥር
እንዴት አብረን እንጋራው?የት ደብቀነው እንደር::
እዱኛ አይሸፍነው እዳ እንደዘር-ውርዴ ውስጥ ውስጡን
በዝንተ-አለም ውጭ-ልክፍት ከትውልድ ትውልድ ተሰደን
ከትውልድ ትውልድ ከስለን
ይኸው እስከዛሬ አለን::
ስሚኝማ ጽጌረዳ
አንቺ ተንሳፋፊ አበባ
አንቺ የልቤ እንባ ቆባ
ምነው በደረሰ አበባሽ
የማንነት ባላንጣ ከውጭ ወደ ውስጥ በሸሸሽ
የአየር አበባነት ቀርቶ ምነው የምድር እምቡጥ በሆንሽ!!
አንቺ አበባ ነይ እንሽሽ
ወደአፈር ወደቀያችን: ነይ እንሰደድ እባክሽ!!
አንቺ እርግብ ስር-አልባ አበባ ነይ ተሰደጅ ወደ እትብትሽ
ወደውስጥ አንራቅ እባክሽ
ወደ አገር እንሽሽ እባክሽ
(ለስደተኛዋ አበባና ወደ አገራቸው ለመሰደድ ለሚሹ)
ከ "የእኛ ሰው በአሜሪካ" መጽሃፍ የተወሰደ
In : Poems