የእኛ ሰው በአሜሪካ በነቢይ መኮንን .... ኒውዮርክ ውስጥ ነው

Posted by Basha BIRU on Thursday, April 22, 2010 Under: Litrature ... Fiction/others
ወደ ኒውዮርክ ልንሄድ በዋዜማው እንደለመድኩት ከአንድ አራት የዲሲ ነዋሪ አበሾች ጋር ለማምሸት ቀጠሮ ይዤ ነበር :: እነሱም የአገር ቤት ወሬ ናፍቀዋል ::እኔም የነሱን አንዋንዋርና ህይወት ለማወቅ ጉዋጉቻለሁ :: ከቅርብ አመታት ወዲህ በዲቪ ወደ አሜሪካ ስለሚወጣ የአገራችን ሰው ጨዋታ ተጀመረ :: በነባሩ አበሻና በዲቪ በሄደው መካከል ልዩነቱን ያወቅኩት ያኔ ነው ::
"የሚገርመው " አለ አንደኛው :: አነጋገሩ ምሬት -ቅልቅል ነው :"ይህ በዲቪ የመጣው መንጋኮ የአሜሪካን መንግስት እዚህ አምጥቶ ቤት ሰጥቶ ,ስራ አስይዞ አንቀባሮ የሚያኖረው ይመስለዋል : ጅል ሁሉ !" አለ ::
እኔም "ታዲያ ምንድነው የሚያደርግላቸው ?" ብዬ በጥሬው ጠየኩኝ ::
"የመኖሪያና የስራ ፈቃድ ካርድ መስጠት !በቃ !ከዛ በላይ ዱዲ አይሰጣቸውም "አሁንም ስሜቱ እንደጎሽ ነው የሚናገረው ::
ሌላው ቀጠለ ::"ሰው እንዴት እንደዚህ እንደሚሆን አይገባኝም ::ለሀገሩ አያስብ ,ውርደት አይገባው ,ባርነቱ አይታየው .. እንዴት እንደዚህ እንደበግ እንደሚሆን አይገባኝም ::በተለይ የሚገርመኝ ደግሞ ነጭ ሽበት አብቅሎ ካረጀ ቦሀላ እየተንጉዋፈፈ የሚመጣው ኢትዮጵያዊ ነው !" እኔ አሁንም አላስቻለኝም ::
"የእናንተና የእነሱ ልዩነት ምንድነው ?'አልኩና ጠየኩኝ ፍርጥም ብዬ ::
"የእኛ ይለያል ::ከፋም ለማም የእኛ በፖለቲካ ስደተኝነት ስር የሚጠቃለል ነው ::ግማሽ በሱዳን ከፊሉ በሞያሌ ከፊሉ በሱማሌ መከራውን አይቶ እዚህ የደረሰ ነው "::
"እነሱስ ?በቦሌ መጥተው ቢሆን :ለምሳሌ ትምህርት መማር አይችሉም ?"አልኩኝ ::
"በጭራሽ እንኩዋን / ስራ እንኩዋን መርጠው ለመግባት የሚያስብ ጭንቅላት የላቸውም !"
"እናንተስ ተምራችሁዋል ?"
"የእኛ እንኩዋን ሪአሊቲው (ነባራዊው ሁኔታ ለማለት ነው )ይለያል ::እኛ አየህ ብዙ አይነት አበሳ የተፈራረቀብን አገር ቤት በእስርና በመሳደድ ከዚያም በሱዳን በረሀ ስንማቅቅ ቆይተን የመጣን ነን :: የብዙ መከራና ያለመረጋጋት ችግር ሰለባዎች ነን ::በዚህ ላይ አገር ቤት የነበረው የፖለቲካ ልዩነት እዚህም አፍጦ አግጦ ነው የጠበቀን :: ተወኝ ባክህ ያየነውን ፍዳ እኛና እግዚሀር ብቻ ነን የምናውቀው !"
ምክንያቱ ምንም አልተያዘልኝም ::ማምለጫ ነው የሚመስለው "አሁን ያልከኝን ጠንፈፍ አድርጌ ሳየው እናንተ ብዙ መከራ አይታቹ እዚህ እንደደረሳቹ እንጂ እዚህ እንዳትማሩም ሆነ ስራ ይዛቹ እንዳትኖሩ ያገዳቹ ነገር በተለይ ዲቪው መንጋ ነው ያልከኝ ?...." ነጠቀኝ ስለዲቪ ሳነሳ ::
"የዲቪ በጎች !በላቸው አትፍራ " አለ ጮክ ብሎ ::
"ብቻ ምንም በልዋቸው : ከእነሱ ጋር በተለይ ያላቹ ልዩነት ቀልቤን አላሸነፈውም "ረጋ ብዬ በለሆሳስ ተከላከልኩ ::
"ነቢይ ከነሱ ጋር ልታወዳድረን መሞከሩ ራሱ ለኔ ወንጀል ነው የሚመስለኝ !ያንን የመሰለ ለኢትዮጵያ ህዝብ ስንት ግፍ የተቀበለ ትውልድ ከዚህ ዝም ብሎ ከሚነዳና ጭራሽ የሚሄድበትን እንኩዋን የማያውቅ አላማ -ቢስ ትውልድ ጋር ማወዳደር እንዲያውም ትልቅ በደል ነው ነው የምለው "
"እኮ አስረዱኛ !እሺ መከራ ፍዳ አያቹ ::ተሰቃይታቹ አሜሪካ ገባቹ ::የመከራው የዞረ -ድምር ነበረባቹ :: ግን ..."አሁንም አንዱ አቁዋረጠኝ ::ወይ ጉድ !በጭራሽ የማዳመጥ ባህል የላቸውም አልኩኝ በሆዴ :: አሰፋ ጫቦ እንደገለጻቸው ዋን ዌይ ሮድ (ለመናገር ብቻ አፍ የተሰጣቸው እና የአንድ አቅጣጫ መንገድ ብቻ ያላቸው ::የሰው መልስ የሚያዳምጡበት ጆሮ ግን የሌላቸው ሌላ መንገድ ሌላ አቅጣጫ ያልተሰጣቸው አይነት ሰዎች ናቸው ) ቀጥለው አሁንም አቁዋረጡኝ ::
"that's it!" አለ አንዱ :: ሁሉም "than't it!.." "that it!.." "that it.." አሉ :: እንደመፈክር ነው የሚያሰግሩት ::
እኔ ግን ሙዝዝ ብዬ ቀጠልኩ "አዎ መከራ ሙሉ በሙሉ አለቀቃችሁም ነበር ::ግን ከጊዜ በሁዋላ ሙሉ በሙሉ ጠፍቶዋል ::እናንተ ግን ወይ ከምር አልተማራችሁም ::ወይ ደህና ስራ አልያዛችሁም ::አልያም ይህን አይነት መፍትሄ ለአገሬ አመጣለሁ ብላቹ ቁርጥ ያለ ስራችሁን አልገለጻችሁም ::ታድያ እንዴት ነው እናንተን የሰማ ሰው በእድል ሎተሪ ከወጣለትና ከመጣው ከዲቪው -አበሻ ይሻላሉ ብሎ ዳኝነት የሚሰጠው !?"
(ለነገሩ በውስጤ እኔም ብመጣኮ እንደነሱ እሆን ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ውስጤን አከክ ሳያደርገኝ አልቀረም )
"አቦ ሌላ ጨዋታ አምጡ አንድ ነገር ላይ "ቦርንግ " አደጋችሁን " አለ እስከአሁን ሳይናገር የቆየው ወዳጃችን :: "አሰለቻችሁን " ነው ነገሩ :: (የእንግሊዝኛውን ቃል አጠቃቀሙ ትንሽ ፈገግ እንድል አድርጎኛል :Smile ነገሩ የመሸነፍና የሽሽት መንፈስ እንዳለበት ቢገባኝም እንግድነቴን አክብሬ ጨዋታው እንዲቀየር መፍቀድ ግዴታዬ ነው :: እኔም የአገሬ ልጅ ነኝና በይሉኝታ እስኪ ይሁን አልኩ ::ሆኖም ሌላ ቀን ማንሳቴ እንኩዋን አይቀርም : አልኩ በሆዴ ::

"ስለሺ ናይስ ሆንዋል አሉ እዛ ?" አለ አንዱ ቀጠለና ::
ጋሽ አበራ ሞላን መሆኑ ገብቶኛል :: ቢሆንም እስቲ ከሱ ይምጣ ብዬ "ማነው ስለሺ ?" አልኩኝ ::
"ስለሺ ነዋ !የእኛ ልጅ !ከዚህ ሄዶ አዲስ አበባን ላጽዳት ብሎ ያተራመሰው ጀግና ::ያንን የተኛ ህዝብ አባነነው አሉኮ !ከኔ ጋር ይገርምሀል ጅቡቲ አብረን ነበርን ::እዚህም ብዙ ግዜ አብረን ነው የቆየነው ::"
"አሁን ግን አብራቹ አይደላቹም !" አልኩ እንደማሾፍ ::
" ወዳጄ ምነው ገብስ ገብሱን ብንጫወት :: እኛ እንዲህ መቼ ደላን ወንድሜ ?ለኛ ለኛ የማርያም መንገድ መቼ አላት ኢትዮጵያ ?"
"that's it.." "that's it..." አሉ ሌሎቹ አውራ ጣታቸውን ቪቫ እንደማለት ቀስረው እየሳቁ :: በጸጥታችን ውስጥ የቢራ መጎንጨት ድምጽ ብቻ ተሰማ :: ለእረፍት ያህል ተለያየን ::
"እኔ የምለው " አልኩ የጸጥታውን በረዶ ለመስበር : የአበራ ሞላ አይነት አንድ አራት ይጠፋል ከድፍን ዲሲ ? ጥቂታቹ እንኩዋን ምናለ ብትመጡ ?"
"ነቢይ እውነት አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራው ስራ ለአንዲት ደቂቃስ ለህሊና እረፍት ይሰጥና ነው ለመኖር አትችሉም ነበር ወይ የምትሉን ?"
"አይ መቼም በጣም ደህይታለች ስራ አጡ መአት ነው በሽታ ድርቅ ብዙ ነገርም ተደራርቦባታል "
"That's it!" አለ አንዱ ::
"ግን ይህን ለማሸነፍ የሚቻልበት መንገድ ይኖራል :: እርግጥ አድካሚ ነው ረዥም ግዜ ይፈጃል ::አበራ ሞላን እንይ እሺ ከራሱ ከእናንተው ጉዋደኛ ልጀምር ..."
" ማይግሬሽየስ !("መድሀኒአለም ይቅር ይበልህ "ነው ነገሩ ) እኔ ምሳሌ ለምን አልሰጥህም ? የኢትዮጵያ ነገር እንዴት ተስፋ እንደሚያስቆርጥ ላስረዳህ ?.. አንዱ ምን እንዳለኝ ታውቃለህ ?... አንድ ግዜ ከአንድ ጉዋደኛዬ ጋር በግል መኪናው ጋቢና ቁጭ ብዬ ስሄድ ለአደጋ መከላከያ እንዲሆን ተብሎ መኪና ውስጥ የተንጠለጠለውን ቀበቶ አንስቼ በትከሻዬ አሳልፌ አጠለቅኩ :: ትንሽ እንደሄድን ትራፊክ አስቁሞ ፖሊስ ጣቢያ ይዞኝ ሄደ :: ሁሉም ሳቁ ከኔ በስተቀር ::
(ወቸው ጉድ !እነዚህ አበሾች ወይ እሚያምኑት ወሬ አጥተዋል :አልያም ሲፈጸም የሚያዩትን ሳይሆን :እንዲሆን የሚፈልጉትን ነው ማመን የሚሹት :አልኩ በሆዴ ) ያም ሆኖ ግብዝነት ነው ብዬ አልተውኩዋቸውም :: ጥያቄዬን ቀጠልኩ ::
"ታድያ አንተ አመንከው ?"
"ኦፍኮርስ ፋክት እኮ ነው !(ተጨባጭ ነገር እኮ ነው !)
"እኔ አንተን ብሆን ቀጣፊ ነህ !ምን አይነት አይን ያወጣ ውሸት ነው የምትዋሸው ?" ነበር የምለው ! አንተም ድፍረቱን አጥተህ ነው እንጂ ውሸት መሆኑ ሳይገባህ ቀርቶ አይመስለኝም !" አልኩት ትንሽ ፈርጠም ብዬ :: ይሄኛው ማላገጥ ከምር አናዶኝ ነበር ::
"በኢትዮጵያ መኪና የአደጋ ጊዜ ቀበቶ ማሰር ምንምንኳ እንደወንጀል ተቆጥሮ ያሳስራል " የሚለውንም አይነት ቅጥፈት አልቀበልም :: ዝም ብላቹ ማዳመጣቹ ማፈሪያ ነገር ነው ለናንተ " አልኳቸው ::"የሀገርን ሁዋላ ቀርነት በዚህ መንገድ መግለጽ ደግሞ ጭፍን ጭካኔ ነው :: ጭቦም ነው !"

In : Litrature ... Fiction/others 


Tags: ethiopians life in america  የእኛ ሰው በአሜሪካ 

If you are unable to see amharic fonts please download most common amharic fonts in downloads catagory or click here.

Make a Free Website with Yola.