የእኛ ሰው በአሜሪካ _በነቢይ መኮንን _ኒውዮርክ ውስጥ (መነበብ የሚገባው እውነት)

Posted by Basha BIRU on Thursday, April 22, 2010 Under: Litrature ... Fiction/others
ኒውዮርክ ውስጥ ::

ኒውዮርክ ከሁሉ ነገርዋ ጎልቶ የሚታይባት የመጤ ዜጋ መብዛት ነው ::"ሁሉን አቅፍ ባይ ናት " እንደመርካቶ :: አበሻም በርካታ አላት ::አብረውኝ የጋዜጣ ህትመት ፕሮግራም ከሚከታተሉት ጓደኞቼ መካከል ከፓኪስታንና ከሲሪላንካ ከመጡት ወዳጆቼ ጋር ኒውዮርክ ጉራንጉር ድረስ ሄደናል :: የኒውዮርክ ገበያ አስገራሚ ነው :: እንደፓሪስ እጅግ ውድ "የሚታይ እንጂ የማይበላ ፍሬ " የሚባለውን አይነት ዋጋው ንቅንቅ የማይል እቃ አለ :: በአንጻሩ እንደመርካቶ 70 ዶላር የተባለውን እቃ ተከራክሮ 23 ዶላር መግዛት የሚቻልበትም ሱቅ አለ ::

አንድ ልቤን የነካኝና ያሳዘነኝ ነገር ግን በተዘዋወርንበት ስፍራዎች ፓኪስታኑ ጓደኛዬ የፓኪስታን ማህበረሰብ አገኘ :: እንደ ጉድ የሚነግዱ ታታሪ ፓኪስታኖች ያሉበት :: ሲሪላንካዊው ጓደኛዬም ተርብ ተርብ የሆኑ የስራ ሰዎች የሆኑ ሲሪላንካውያን ተደራጅተው የልብስ የጫማ ስፌት የአሮጌ ቴፕ እደሳ ንግድ ያጡዋጡዋፉበት ቦታ ወሰደኝ :: "ኢትዮጵያውያንስ የት ነው ስራ የሚሰሩት ?ኮሚኒት አላቸው አደል ?" ብለው ቢጠይቁኝ አይኔ ፈጠጠ :: ቅስሜ ተቀጨ :: ከዛ ሁሉ በሺዎች ከሚቆጠር እኔ ካየሁት አበሻ ተደራጅቶ ስራ የሚሰራ የለም እኔ እስከማውቀው ድረስ :: ተነጣጥሎ ተነጣጥሎ የቀን ሞያተኛነት ስራውን ሊሰራ ይበታተናል :እንደሚታወቀው የሚሰባሰበውም ለወሬ ብቻ ነው - የፈረደበት የአበሻ ሬስቶራንት ውስጥ :: የጉዞ ጓደኞቼን የትም ልወስዳቸው ባለመቻሌ እዛው አበሻ ሬስቶራንት ወስጄ ራት ጋበዝኩዋቸው :: ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጥፋ ነው መቼስ :: ወደ ሆቴሌ ስመለስ ገና ኒውዮርክ እንደገባሁ ደውዬ መልእክት ትቼላቸው ከነበሩ ወዳጆቼ መካከል መልስ የሰጠኝ የአንዲት አክስቴ ልጅ ባልና ኢብሳ ጉተማ የኦ ኤል ኤፍ አመራር አባል ይገኙበታል ለሁሉም የመልስ ምት ደወልኩኝ :: አቶ ኢብሳን ለጊዜው አላገኘሁትም መልእክት ተውኩለት ::

የአክስቴን ልጅ ባል አገኘሁት ::
አማቼ ልበለውና ከአማቼ ጋር ማታውኑ ተቃጠርን :: በአንድ የአበሻ ሬስቶራንት ውስጥም ተገናኘን ::
"እዚህ ጥሩ ጠጅ ይሰራሉ እስቲ ሞክረው :: የአሜሪካን ጠጅ ቀምሰኸዋል ?"
"አረ አልቀመስኩትም !" አልኩት ::
"በል አሁን ቅመሰው :: ሄደህ ለእነ ይገባዋል ጠጅ ቤት ለእነ ቀስቶ : ለእነ ጎንደር ጠጅ ቤት ትነግርልናለህ !"
"ይሄን ሁሉ የጠጅ ቤት ስም ማስታወስህ ይገርማል ::"
"ሌላ ምን ስራ አለን :: አሜሪካን ቁጭ ብለን በትዝታ ነውኮ የምንኖረው ትናንትን እየከለስን "
ጠጁ ታዘዘና መጣ :: ዘይት ይመስላል - ጥልል ያለ መነን ዘይት !! በጠርሙስ ነው የሚሸጠው አንዱ 10 ዶላር ያወጣል :: ገና ለማጣጣም ሁለት ስጎነጭ አናቴ ላይ ወጣ :: ማስከሩ ነው እንጂ የአገሬን ጠጅ ጠጅ አይልም :: ማሩ ከሀገራችን ነው የሚመጣው ::ስኳሩም ያው ስኳር ነው :: ታድያ ምን እንዲህ ጣእሙን አጠፋው ? ከውሀው ይሆናል አልኩና እንደ እንጀራው አስታመምኩት :: ከዚያ ስለ ሀገር ቤት ጠየቀኝ :: ብዙ አመት በአሜሪካ እንደቆየ አስረዳኝ :: እንደብዙ አበሻ ማንሀታን የጥቁሮች መንደር አካባቢ እንደሚኖር :
ሌሎችም ብዙ ወደ ክዊንስና ብሮንክስ እንደሚኖሩ አስረዳኝ ::
"ለመሆኑ ኑሮ እንዴት ነው አልኩት ?"
"ጥሩ ነው ምንም አይልም " መለሰልኝ ::
"እዚህ ብዙ የአበሻ ሬስቶራንት አለ እንዴ ?"
"እንደዲሲ አይሆንም እንጂ አለ "
"ምንድነው እንደዲሲ እንዳይሆን ያደረገው ?ብዙ አበሻ የለም እንዴ ?"
"እንደ ዲሲ አይሆንም :: እዚህ የሌለ አይነት ዜጋ የለም :: ጥቁር ነጭ ቡናማ ቢጫ ቀለም ያለው .... የሰው ዘር የተባለ ሁሉ አለ :: አበሻም አለ ግን እንደ ዲሲ በዞርክበት የምታገኘው አይነት አይደለም ::"
"ኑሮውስ እንዴት ነው ?"
"አወዳድረን ስናየው ውድ ነው !"
አንድ ጥያቄ ለመጠየቅ ስፈራ ስቸር ቆይቼ
"ለመሆኑ ከኢትዮጵያ ከመጣህ ተምረሀል ?ብዙዎቹ አበሾች ስለትምህርት ሳነሳ ወይ ይከፋቸዋል መማር ምን ያደርጋል :ተምረህም ኩሊ ነው የምትሆነው የሚል አመለካከት ነው ያላቸው " አልኩት ::
"እኔ መጀመሪያ ወደ አሜሪካ ሳይሆን ወደ አውሮፓ ነው የተሻገርኩት :: እዛ ማስተርሴን ሰራሁ :: እኔ ያለትምህርት የትም ይደረሳል ብዬ አላምንም :: ከሀገሬ ወጥቼ በስደት መከራን የማየውም ለመማር ብዬ ነው ::"
"ተባርክ !" አልኩት በሆዴ ::
"ከዚያስ አሜሪካን መጥተህ እንዴት ሆንክ ?"
"!አሜሪካና አውሮፓ በጣም ይለያያል :: እዚያ የማህበራዊ ዋስትና ገንዘብ ይሰጥሀል :: እዚህ ዱዲ ቀይ ድንቡሎ የሚሰጥህ የለም :: አፈር ግጠህ ዶላርህን ታጠራቅማለህ :: በቃ ትኖራለህ :: አውሮፓ ከፈለክ ዝም ብዬ ልደንስ ካልክ ተኝተህ ትበላለህ :: ስደተኛነትህን የምታስታውስህን ያህል ጥቂት ገንዘብ ይሰጡሀል ከወር ወር አብቃቅተህ እስዋን እየቆረጠምክ ለጥ ልትል ትችላለህ :: እዚህ እንዳልኩህ እስከ መጨረሻዋ የላብ ጠብታ ሰርተህ ደም ተፍተህ ነው መኖር የምትችለው :: ከለፋህ ጥሩ ትኖራለህ ::"
"ካልለፋህስ ?"
"ተጨንቀህ ተደብረህ ትሞታለህ "
"ብትሰራስ ጭንቀት ይቀርልሀል ማለት ነው ?"
"አየህ የጭንቀት ጫና እኛም ላይ ነጩም ላይ አለ :: እርግጥ የኛ ይብሳል ::"
"ለምን ?"
"እኛ "አይደንቲቲ ክራይሲስ "(የማንነት ረሀብ ) አለብን :: እትዮጵያዊ ነን እንዳንል እንደፈረንጁ ካልሆን እያልን መከራ እናያለን :: ፈረንጅ እንዳንሆን በጭራሽ የአበሻ ልጅነታችን ይጎትተናል ::"
"እስቲ የአውሮፓውን የማንነት ረሀብና የዚህ አገሩን አወዳድርልኝ "
"ይገርምሀል አውሮፓ ነጭ ነጭ ነው ጥቁር ጥቁር ነው ::"
"እኔም አውሮፓን አይቸዋለሁ :: እንዳልከው ነጭ ነጭ ነው :: ጥቁርነትህን ቶሎ ይሰማሀል :: እንዲሰማህ እያደረጉህ ነው ? ወይስ አንተም በጥቁርነትህ ትንሽ የዘረኝነት ስሜት አያጣህም ?"
"ኢን ዌይ ልክ ነህ :: እኛም ነጩን ስናይ ወዲያው ጥቁርነታችን ፍጥጥ ብሎ ይወጣል :: እኛ እንግዲህ በአረብና በሌላው ጥቁር አፍሪካዊ መካከል ነን የሚል የቡና አይነትነት የበላይነት (የምርጥነት ) ስሜት በውስጣችን አለ :: ነጩ አጠገባችን ሲኖር ግን ወዲያው ባልጩት መስለን ቁጭ እንላለን :: ልባችንን ጭምር ጥቁርቁር እናደርጋለን :: ስለዚህ ነጩ ነጭነቱ የሚናገርበት አፍ ብቻ አይደለም ያለው :: ቴክኖሎጂ አለው :: ትላልቅ ቡና ቤቶችና ሆቴሎች አሉት :: እነዚህ ጥቁርነትህን ይነግሩሀል :: መቶ ግዜ ኪስህን ብትቡዋጥጥም የምታወጣው ገንዘብ በጭራሽ የማይደፍራቸው ውድ ውድ ቦታዎች አሉ :: የቡና ቤቶቹ ቦዮች ሳይቀሩ እንዴት እንደሚንቁህ ታያለህ :: በግልጽ !አውሮፓ በግልጽ ስደተኛ ነህ ይሉሀል :: ቁርጥህን አውቀህ ቁጭ ትላለህ !"
"አሜሪካስ ስደተኛነትህ እንዳይታወቅህ ያደርጋል እንዴ ?"
"በጭራሽ :: አሜሪካንም ያሳውቅሀል :: ግን እንዳሳወቀህ አያሳውቅህም በአብዛኛው ሽፋን አለው "
"እንዴት ቢያንስ አንተ ራስህ ጥቁርነትህን ስደተኛነትህ ይታወቅህ የለም እንዴ ?"
"አንተማ አዎ :: ግን እንግሊዝ ጀርመን ፈረንሳይ ገና ሲያይህ ሲቀፈው ይታወቅበታል :: እሱ የገባበት ሆቴል እንዳትገባ ይፈልጋል :: እሱ የሚከፍለውን ያህል ስትከፍል ቢያይ ደሙ ይፈላል ::
አሜሪካ እሱ የሚከፍለውን ያህል ስትከፍል ቢያይ ገንዘቡን ወደ አገርህ ይዘሀት እንዳልሄድክ በማየት ይደሰታል :: አሜሪካ ውስጥ ጨፍር ደንስ እበድ ጉዳዩ አይደለም :: ናይት ክለቡን ጭፈራ ቤቱን ጌቶውን ሐርለሙን ሐሺሹን ራቁት ዳንሱን መደሰቻ ቤቱን ሁሉ ነው የሚያመቻችልህ :: ከሀገሩ ቤሳ ቤስቲን ይዘህ እንዳትወጣ ነው :: ጉልበትህን እንጂ አንተን አይፈልግህም ::ግን እንደደረጃህ (ከቀናህም ከሰው በላይ )እየቀበጥክ እየዘለልክ እንድትኖር ይፈቅድልሀል ::ልክህን ያውቀዋል :: ግን ልክህን የሚያሰምርልህ በሆዱ ነው : ሽሽግ ነው የምልህ ለዚህ ነው ::
"እንዳይታወቅ ያደርጋል ማለት ነው አውቆ ?"
"... ኖት ኢን ዌይ ... ምን መሰለህ ማንም አሜሪካዊ ሲስተሙ -ስርአቱ አንተን ልክ እንደሚያገባለት ያውቃል :: ለምሳሌ ብታድግ ብታድግ ምን ችሎታ ቢኖርህ ከሱ እኩል እንድትሆን አይፈቅድም ስርአቱ :: ያግድሀል :: ቢሮ ገብተህ በወግ ተቀምጠህ ከእሱ እኩል ኮርተህ ስራ የመስራት እድል የሚያጋጥምህ ከስንት ሺህ አንድ ብቻ እንደሆነ አሳምሮ ያውቃል :: የጉልበት ስራውን ግን የሚከለክልህ የለም :: እሱ ሚልዮን ዶላር ለምን አታፈራም አይመቀኝብህም ::አንተ የተፈጠርከው ለዚህ ነው ማለቱ ነው ! አሜሪካ በድንበር ተሰደህና በቦሌላ በባሌ ጉልበትህን ይዘህላት እንደመጣህ ስለምታውቅ እኔ የአለም ልጆች እናት ነኝ :: ሁሉም እኔ ውስጥ ተስማምተው ይኖራሉ ትልሀለች :: ዶላር ሳይሆን ጉልበትህ ይዘህ እንደመጣህ አሳምራ ታውቃለች :: ብዙ ለፈለፍኩብህ .... ብሶቴን አንተ ላይ የማራግፍ መሰለኝ ? እስቲ አንተ ተጫወት ነቢይ ?"
"በጣም ተስማምቶኛል :: ቀጥል ግድ የለህም :: አስተያየትህም ሆነ የተሰማህ ስሜት ዲሲ ካጋጠሙኝ አበሾች ይለያል :: ....ስለ አበሾች የአእምሮ ጭንቀት ጫና ስታነሳ ምን ትዝ አለኝ መሰለህ ? አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ "ቴዲ አፍሮ " የተባለው ዝነኛ ወጣት ዘፋኝ ይዘፍናል ተብሎ በሺዎች የሚቆጠር ተመልካች ይታደምልሀል :: በመሀል ምን እናያለን የቀይ መስቀል መኪና :: ይህ ደግሞ ለምን መጣ ? ብዬ አንዱን ወጣት ጠየኩት :: "ማይክል ጃክሰን ሲዘፍን አድማጩ "ፌንት " አድርጎ ሲወድቅ : ሌላም ፈረንጅ ሲወድቅ አይተው የቴዲ አድናቂዎችም ፌንት አድርገው እንዳይወድቁ ተፈርቶ ነዋ ! አበሻኮ ፌንት አድርጎ ወድቆ አያውቅም :: ! ስትሬስ ምናምን በጭራሽ አይነካውም ! አለና በሳቅ ገደለን ::....

"አሁን ትምህርትህ ምን ደረሰ ?"
"አሁንማ በህክምና ዶክትሬቴን ጨርሻለሁ ::"
" ሀኪም ነሀ ! የት ትሰራለህ ?
"እሱ ነው ጉዱ !"
"እንዴት ?"
"አሜሪካን ሀገር የህክምና ዶክትሬትህን ትይዛለህ እንጂ በቀጥታ ሀኪም ትሆናለህ ማለት አይደለም ::"
"አልገባኝም :: ስራ በቀላሉ አይገኝም ?... ማለቴ አይቀጥሩህም ወይስ ...."
"ዌል .... እንደሱ ነው ማለትም ይቻላል :: ግን ....
አሁን ግራ ገባኝ :: እነዚህ አበሾች ስራ ሲደርሱ አፋቸውን የሚይዛቸው ነገር አለ !::
"ምንድነው ችግሩ ?በተማርከው ትምህርት ስራ መስራት ክልክል ነው እንዴ ?
"አረ በጭራሽ ?"
"ታዲያ ... አንተ ለምሳሌ አሁን ምን ትሰራለህ ?"
"ይሄውልህ ነቢይ :: ከምኖርበት ከተማ የምሰራበት ቦታ ድረስ የአንድ ሰአት ተኩል ያህል ጉዞ ነው :: እዚያ ድረስ እየነዳሁ ሄጄ ነው ስራ ስሰራ ውዬ የምመለሰው :: ትምህርቴን ከጨረስኩ ወደ 3 አመት ገደማ ሆኖኛል :: እየተማርኩ እያለሁ ሆቴል ማስተናገድም ፓርክ ላይ መኪና ማስተናገድም የጉልበት ስራ አንዳንዴ ሳገኝ ደግሞ /ቤት ውስጥ ለዶክተሮቹ ረዳትነትም እሰራ ነበር ::"
"አሁንስ ?"
"አሁን የምሰራበት እንዳልኩህ አንድ ሰአት ተኩል የመኪና ጉዞ ቦሀላ የሚገኝ አንድ ሆስፒታል አለ ...."
"!አንተ ታድለሀል ቢያንስ በተማርከው ትምህርት ነው ስራ የምትሰራው !...."
"ነውም አይደለምም "
"ለምን .... ነው እንጂ !"
"አየህ አሁን ለጊዜው የምሰራው በሽተኞች ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ ተራ ማስያዝ ነው :: ማሰለፍ በለው ...."
እኔ ለትንሽ ግዜ ጸጥ አልኩኝ :: ትንፋሽ ያጠረኝም መሰለኝ ::
"ለመሆኑ በሽተኛ ስታሰልፍ መዋሉን ህሊናህ እንዴት ተቀበለው ?" አልኩት ከአፍታ ረፍት ቦሀላ ::
"ምን ታደርገዋለህ ! ባትቀበል የት ትደርሳለህ ? አየህ ቀስ ቀስ እያልክ ወደ ሙያህ እየተጠጋህ ትሄዳለህ :: ላትደርስም ትችላለህ :: እንደውም አብዛኛውን ጊዜ Asymptotic graph አይነት ነው (በሂሳብ /ርት መስመሩ ይጠጋል እንጂ አይነካም የሚባለውን ግራፍ አይነት ማለቱ ነው )

In : Litrature ... Fiction/others 


Tags: ethiopians life in america  የእኛ ሰው በአሜሪካ 

If you are unable to see amharic fonts please download most common amharic fonts in downloads catagory or click here.

Make a Free Website with Yola.